በኮሞሮስ ሲቪል አቪዬሽን እና ሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና በሀገሪቱ ኤርፖርቶች ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ህዳር 1 ቀን 2015 ዓ.ም በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሥራ ጉብኝት አደረጉ፡፡
የኮሞሮስ ኤርፖርት ኩባንያ ዳይሬክተር ማሞን ቻኪራ እና የሲቪል አቪዬሽንና ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ናሱር ቤን አሊ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ቢሮ ተገኝተው በተደረገው ውይይት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡ በእለቱ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ስልጠና አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በቀለ በአካዳሚው እየተሰጡ ስላሉ የስልጠና ይዘቶችና አጠቃላይ ስርዓቱ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከልዑካን ቡድኑ ለቀረበላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ሰብሳቢነት ከኮሞሮስ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይት ሁለቱም ወገኖች በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ ረቂቅ አዘጋጅተው ልውውጥ እንደሚያደርጉና በረቂቁ ላይ ስምምነት እንደደረሱ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ሰነድ ፈርመው በቀጣይም በትምህርትና ስልጠና፣ በኮንቲንጀንሲ ፕላን አዘገጃጀትና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር እንደሚሰሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡