የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የግሉ ዘርፍ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ የሚኖረውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራረሙ፡፡
ህዳር 7 ቀን በኮሚሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የፊርማ ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ “ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ጥቂት ሀገሮች ውስጥ አንዷ ብትሆንም ከዘርፉ ሊገኙ ከሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ማለትም አቪዬሽን ቴክኖሎጂ፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ቱሪዝም እና ሌሎች የኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ፣የኤርላይን ኢንዱስትሪ፣ አቪዬሽን መሰረተ-ልማት፣ በኤርካርጎ፣ በሜንቴናንስ፣ ጄኔራል አቪዬሽን ፣ እና ሌሎች በርካታ መሰል፣ ዘርፎች ላይ ያለን ድርሻ እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ነው” ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ዘርፉ ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠር የሚችል አቅም ያለው ሲሆን ይህንና ሌሎች ጥቅሞችን በአግባቡ በመጠቀም ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮና ፣ ቱኒዚያ ከዘርፉ ከአፍሪካ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶትና የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በቀጣይ የግሉ ዘርፍ በአቪዬሽን ሊኖረው የሚችለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ሁለቱ ተቋማት በርካታ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ክብርት ወ/ሮ ለሊሴ ነሜ በኩላቸው ኮሚሽኑ በአዋጅ 1180 ከተቋቋመ ጀምሮ የኢንቨስትመንት ልማት መስኮችን በመለየት የግሉን ዘርፍ አስተዋፅኦ ማጎልበትን ዋንኛ አላማው አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ገልፀው “በተለይ በኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ገብተው እንዲሰሩ ማበረታታት ያስፈልገናል” ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መግቢያ በር ነው ያሉት ኮሚሽነሯ ዛሬ የተፈረመው ሰነድ ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡